Tuesday, April 15, 2014

ዶሮዋን አታታሏት፤ በመጫኛም አትጣሏት!!

በማስረሻ ማሞ (ሆላንድ)

በአንድ አገር ላይ አብዮት የሚከሰተው ምን ሲኾን ነው? አብዮቶችስ ወደ ዐመጽ የሚቀየሩት ምን ዐይነት ተግዳሮት ሲገጥማቸው ነው? አብዮት በአንድ አገር ላይ ሥር ነቀል ለውጥ ለማምጣት ያለው አበርክቶትስ ምንድን ነው?

የየትኛውም አብዮት መነሻ ምክንያቱ ጭቆና ነው። የኢ-ፍትሃዊነት ሥር መስደድ ነው። የመልካም አስተዳደር እጦት መስፋፋት ነው። የአንድ አገር ማኅበረሰብ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚ በጥቂት ጉልበተኞች ቁጥጥር ሥር መግባት ውጤት የሚፈጥረው እልህ ነው። በተቀመጠው ሕገ-መንግሥታዊ መስፈርት መሠረት መንግሥት ዜጎችን በእኩልነት መምራት ሲሳነው የሚፈጠር የታመቀ ጭቆና የሚፈነዳበት ክስተት ነው።

በዚህ ሰዓት ስለ “ቀለም አብዮት ሰላባዎች” ዶክመንታሪ ፊልም አሰርቶ የሚያሳየን ኢሕአዴግ ባንድ ወቅት አብዮተኛ ነበር። ዛሬ አብዮት ምን ያህል አስከፊ ነገር ሊያመጣ እንደሚችል በእነ ዩክሬን በኩል እያሳየ ሊያስረዳን ይሞክራል። የዚህ አብዮት አራማጆች ደግሞ ምዕራባውያን (የኒዮ ሊበራል አጀንዳ አራማጆች) ናቸው ይለናል። በዩክሬን እና በመሰል አብዮቶች ውስጥ ምዕራባዋያን እጃቸውን አይጠልቁም ማለት አይቻልም። ምዕራባውያን ብቻ ሳይኾኑ፤ የእነሱው ተቃራኒ ርዕዮተ ዓለም የሚያራምዱት እነ ሩስያም ባመቻቸው መንገድ እጃቸውን ይነክራሉ። ይኼ በዓለም ፊት የበላይነትን ለማስረገጥ የሚደረግ የሥልጣን ጫዎታ ነው። ዶሮዋን አታታሏት፤ በመጫኛም አትጣሏት!!

በዚሁ የኢቲቪ የቀለም አብዮት ሰለባዎች ዶክመንታሪ ላይ ሁለት አዳዲስ ፊቶች ዐየን። መርከብ ነጋሽን እና አቤል አባተን። ርግጥ ነው ፌስቡክ ላይ ይታወቁ ነበር። የሚሰጡትን ትንታኔ ልብ ብዬ አደመጥሁት። ሐሳባቸው እንደተቆረጠባቸውም ገመትሁ። ከፊት ለፊታቸው የተደቀነው የኢቲቪ ካሜራ እንደልባቸው የሚያስቡትን ሁሉ እንዲያፈሱ የሚያደርግ እንዳልኾነም እሙን ነው። ራሳቸውን በደንብ አድርገው በሴንሰርሺፕ ያጠሩትም መሰለኝ። ጥሩ ጎኑ እንዲህም መናገር የሚችሉ ወጣት ልጆች መኖራቸው ነው። ትንታኔያቸው “የቀለም አብዮት ማሰብም ኾነ እንዲደረግ መመኘት ኢትዮጵያን እንደ ዩክሬን ያደርጋታል” ለሚለው የፊልሙ ጭብጥና የመንግሥት አጀንዳ ሰለባ ከመኾኑ በቀር።


ይኼን ጽሑፍ የምጽፈው ልጆቹ አንዲህ ማለታቸው ልክ ነው ወይም ልክ አይደለም ለማለት አይደለም። የዚህ ዶክመንተሪ በዚህ ሰዓት መሠራት ዋና ዓላማ ምንድን ነው የሚለውን ለማየት ነው። የፕሮግራሙ (የፕሮፖጋንዳው) ዋና ማጠንጠኛ ከሚቀጥለው ምርጫ በፊት “ይህ ዐይነት የአብዮት ሐሳብ” ያለው ቡድን ካለ ከወዲሁ አርፎ ይቀመጥ የሚል ማስገንዘቢያ እና ማስፈራርያ ነው። በቀለም አብዮት ሥርዐት ለመቀየር የሚፈልጉ ካሉ “ኢትዮጵያም ልክ እንደ ዩክሬን” ትበታተናለች ነው። ስለዚህ እንዳትበታተን የምትፈልጉ ከኾነ አርፋችሁ የልማታዊ ዲሞክራሲውን ሥርዐት አሜን ብላችሁ ተቀበሉ የሚል መልእክት ያዘለ ነው።

ወይዘሮ ሚሚ ስብሃቱ ምዕራባውያኑ በኢትዮጵያ የመሬት ፖሊስ በጣም ይናደዳሉ ትላለች። ‘መጥተው መግዛት ይፈልጋሉ፤ ለአየሩ ብቻ ሲሉ መሬት መግዛት የሚፈልጉ ምዕራባውያን ኀያላን አሉ። 80 ሚልዮን ለእነሱ ገበያ ነው። እዚህ መጥተው እንደዚህ ማድረግ ባለመቻላቸው ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋራ ግጭት ውስጥ ከቷቸዋል።’ ትላለች። የሚሚን ትንታኔ መቀበል ቢከብደኝም፤ ኢሕአዴግ አሁን መሬት እየቸበቸበ ያለው ለእነማን ነው የሚለውን ጥያቄ ግን አጭሮብኛል። ብዙዎች ዜጎች ከመሬታቸው ላይ እየተፈናቀሉ መሬታቸው ለአረብ ቢልየነሮች የሚሸጥ ከኾነ ምዕራባውያኑን ከመግዛት የሚያግዳቸው ምን አዲስ ነገር ይኖር ይኾን? የአብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥያቄ መሬት የሕዝብ ይኹን የሚል ነው። “ባለራዕዩ” ሰውዬ ደግሞ በመቃብሬ ላይ ካልኾነ አላደርገውም ብለው አፍረጥርጠው ነገርነውናል። ምንም እንኳ መቃብር ተጭኗቸውም ባይሳካልን።

በአንድ አገር ላይ የቀለምም ይኹን የፍራፍሬ አብዮት የሚከሰተው ከሕዝብ ፍላጎት እና ጥቅም በተጻረረ መንገድ መንግሥት ያሻውን ማድረግ ሲጀምር ነው። አብዮት የማይነሳው ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎች ብቻቸውን መልስ ስላገኙ ብቻ አይደለም። ኢኮኖሚ ዋናውን እና ቁልፉን ሚና የሚጫወት ቢኾንም፤ መሠረታዊ የኾኑት የዲሞክራሲ እና የነጻነት ጥያቄዎች እስካልተመለሱ ድረስ ስጋቱን ማቆም አይቻልም።
የአብዮቶች መነሻ ኒዮ ሊበራሊዝም ነው የሚለውን ወደ ጎን እንተወው እና ወደ ኢትዮጵያ እውነታ እንመለስ።

ኢትዮጵያ ውስጥ ከዚህ በሁዋላ አብዮት ሊነሳ ይችላልን?

ለአንድ አብዮት መነሳት ዋነኛ ምክንያቶች ከሚባሉት ውስጥ ጭቆና አንዱ ነው። ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ በአውራ ፓርቲነት እያስተዳደረው የሚገኘው መንግሥት ከአመለካከቱ እና ከአስተሳሰቡ ውጪ የኾነ አቋም እና አስተሳሰብ ያላቸውን ዜጎች ያስራል፤ ይደበድባል፤ ከአገር ያባርራል፤ ራሴ እመራበታለሁ በሚለው ሕገ መንግሥት ውስጥ የሰፈሩትን ዲሞክራሲያዊ እና ሰብአዊ መብቶችን ይጥሳል። ዜጎች ለረጅም ዓመታት ሀብትና ንብረት ካፈሩበት ቦታ ሲፈናቀሉና ቤት ዐልባ ሲኾኑ ዐይቶ እንዳላየ ያልፋል። ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በየትኛውም የኢትዮጵያ ክልል ላይ ተዘዋውሮ የመሥራት መብቱ በክልል ባለሥልጣናት ሲደፈር ዝም ይላል።

አንድ አገር አስተዳድራለሁ የሚል መንግሥት ዜጎቹ ጥቃት ሲደርስባቸው ዝም ሲል ዜጎች ማኩረፍ እና ልባቸውን ማራቅ ይጀምራሉ። እኩል በተፈጠሩበት አገር ባይተዋርነት ሲሰማቸው ይህን ጨቋኝ መንግሥት ጊዜና አጋጣሚ ጠብቀው ሐይሉን ሊነጥቁት ይፈልጋሉ። ይህ በማንም ሰው በኾነ ሰው ውስጥ ያለ ተፈጥሯዊ ስሜት ነው። ጭቆናን እስከተወሰነ ጊዜ ድረስ ተሸክሞ መሄድ ይቻላል፤ ጽዋው ሞልቶ ሲፈስ ግን፤ መመለስ አይቻልም።

የኢትዮጵያ መንግሥት በአሁኑ ሰዓት ለኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ብልጽግና እና ልማት ነው የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሷል። ዜጎች በኢኮኖሚ ራሳቸውን ከቻሉ በሁዋላ የነጻነት እና የዲሞክራሲ ጉዳይ ቀስ ብሎ የሚደረስበት ጉዳይ ነው በሚል እምነትም እየተንቀሳቀሰ ነው። ይህ አካሄድ እና ሃልዮት እርስ በርሱ የሚጋጭ ነው። አጠቃላይ የአገሪቱ ኢኮኖሚ በፓርቲው ሰዎች እና በተመጽዋቾቻቸው ማሽን ውስጥ እየተሽከረከረ፤ 80 ሚልዮኑን ሕዝብ ተጠቃሚ ሊያደርግ የሚችልበት ምንም ዐይነት የኢኮኖሚ ሥርዐት አልተዘረጋም። ኢትዮጵያ ውስጥ የተረጋጋ የኢኮኖሚ ሥርዐት ላለመኖሩ ብዙ ማሳያዎች አሉ። ከምሥራቅ አፍሪካ አገራት ውስጥ በኢኮኖሚ ስደተኞች ብዛት ኢትዮጵያ የመጀመርያው ረድፍ ላይ ትገኛለች። በአረብ አገራት የተከሰተው ግፍ እና በደል የኢኮኖሚ ስደተኝነት ያመጣው ጣጣ ነው። ከ25 እስከ 30 ሺህ ዶላር የሚገመት ገንዘብ ከፍለው በአውሮፓ እና አሜሪካ የውሸት ትዳር የሚያፈላልጉ ሰዎች ብዙ ናቸው። 30 ሺህ ዶላር ያለው ሰው ኢትዮጵያ ውስጥ ከመሥራት ይልቅ ለሚያገባው/ለምታገባው ሰው ለመክፈል ለምን መረጠ? አድጓል ተብሎ በሚወራለት ኢኮኖሚ ውስጥ ይህን ያህል ዶላር አትራፊ በኾነ ቢዝነስ ውስጥ የማያሳትፍ ከኾነ የኢኮኖሚ ሥርዐቱ ለመታመሙ ጥሩ ማሳያ ነው። ይህ በአንድም ኾነ በሌላ መንገድ አለ የሚባለው ዕድገት የይስሙላ ብቻ እንደኾነ ያረጋግጥልናል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ አንድ በጣም አስገራሚ ነገር ላስታውስ፤ የቀለም አብዮትን የሚያራምዱት ምዕራባውያን ናቸው የሚል ክስ ሰምተናል። ከ70 በመቶ በላይ የሚኾነውን የአገሪቱን ኢኮኖሚ የተቆጣጠሩት የመንግሥት ባለሥልጣናት እና ሽርኮቻቸው ግን በእነዚሁ በሚወቅሷቸው አገራት ውስጥ ኢንቨስት ማድረግ ከጀመሩ ሰንብተዋል። በዚያ በኩል ከኢትዮጵያውያን ዜጎች መሬት እየቀሙ ለሕንድ እና ቻይና ይሸጣሉ፣ ይሰጣሉ፤ በዚህ በኩል ደግሞ እነርሱ በኒዮ ሊበራሎቹ ምድር ላይ አንድ ነገር ቢከሰት ብለው የመውጫ ስትራቴጂ ነድፈው ይንቀሳቀሳሉ። ይህ በአገር ሀብት ላይ የተመሠረተ ኢ-ፍትሃዊ የኾነ የሀብት ክፍፍል ጥቂቶች በሚልዮን ብር ዓለማቸውን የሚቀጩ፤ ብዙዎች ደግሞ ከእጅ ወደ አፍ የኾነውን ኑሮ ለመሙላት የሚኳትኑበት የኢትዮጵያ እውነታ ነው። ለፖለቲካና ለፕሮፖጋንዳ ፍጆታ ሲኾን “ከበርቴ መኾን ወይም የከበርቴ ሥርዐትን መከተል” ኩነኔ ኾኖ ይገለጣል። በተግባር ግን አገሪቱን የሚዘውሯት ሰዎች በውጪውም ዓለም ከበርቴነታቸውን እያስፋፉ ነው። ስለዚህ ፈጠነም ዘገየ አብዮት ሊመጣ ይችላል። የሚመጣው ግን ኒዮ ሊበራሎች ስለሚደግፉት እና ስለሚያራግቡት ብቻ አይደለም። የሕዝቡ ጭቆና ስለሚወልደው ነው። ለረጅም ጊዜ ካሉት በታች፤ ከሞቱት በላይ ኾኖ መቆየት ይቻላል፤ ነገር ግን እንደዚያ ኾኖ እስከመጨረሻው መቀጠል የሚሻ ማህበረሰብ ሊኖር አይችልም። አብዮት የሚከሰተው ጎረቤትህ ስለነገረህ ብቻ አይደለም፤ ራስህ ጭቆና በቃኝ የምትልበት የእድገት ደረጃ ላይ ስትደርስ ነው። ነጻነቴን በእጄ ማስገባት እፈልጋለሁ የሚል ውሳኔ ላይ ስተደርስ ነው። ሕዝብ እዚያ ደረጃ ላይ ሲደርስ ያኔ አብዮት ይኾናል።

አብዮት የራሱ የኾኑ አሉታዊና አዎንታዊ ገጽታዎች አሉት። አብዮት በጨቋኝ እና በተጨቋኝ መካከል የሚደረግ ግብግብ ነው። ጨቋኙ ፍጹም አምባገነን ከኾነ አብዮቱ በአጠቃላዩ ማሕበረሰብ ላይ አስከፊ የኾነ ጠባሳ ጥሎ ያልፋል። ፍጹም አምባገነን የኾኑ መንግሥታት በተፈጥሯቸው ሕዝብ የሥልጣን ምንጭ ነው ብለው ማሰብ ስለሚያቆሙ፤ አብዮትን ለመቀልበስ አፈሙዛቸውን ያዞራሉ። በጉልበታቸው፣ በመሣርያቸው፣ በሥልጣናቸውና በገንዘባቸው ይመካሉ። በ97 ዓ.ም በዐይናችን በብረቱ እንዳየነው፤ ሕጻናትን ሳይቀር በአደባባይ የጥይት ራት ያደርጋሉ። ዳግም ይህ ዐይነቱ ጥያቄ እንዳይነሳ እስከመጨረሻው ለማኮላሸት ጭካኔያቸውን እውን ያደርጋሉ። ሥልጣናቸውን ለአገር አንድነት፣ ደህንነትና ለሕዝብ ጥቅም ከመዋል ይልቅ የግል ፍላጎታቸውን ለማሟላት ስለሚጠቀሙበት የምርጫ ካርድ ይዞ ለወጣው ሕዝባቸው ጥይት የሚተፋ አፈሙዝ ይዘው ይጠብቁታል። በአንጻሩ ሥልጣኑን የተቆጣጠሩት ለዘብተኛ አምባገነኖች ከኾኑ አብዮቱ ሊፈጥረው የሚችለውን ቀውስ ግንዛቤ ውስጥ በመክተት ከሥልጣናቸው በትንሹ ቆርሰው በመስጠት ለመደራደር ይሞክራሉ። ይህንን መለስ ያለ አዎንታዊ ገጽታ ልንለው እንችላለን። ትልቁ አዎንታዊ ነገር ግን ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ጨቋኝ አገዛዝን ማስወገድ መቻሉ ነው።

ምንም እንኳ ኢቲቪ አብዮቶች ሁሉ አገር የሚያጠፉ እና የሚበታትኑ ናቸው ብሎ ሊያሳምነን ቢሞክርም፤ ዓለም ላይ ስኬታማ የኾኑ አብዮቶችን በታሪክ ዐይተናል። የፈረንሳውያኑ አብዮት፣ የኢራኑ፣ የኪዩባው፣ የራሺያው የኦክቶበር አብዮት፣ እና ሌሎችም። እነዚህ አብዮቶች እያንዳንዱን አገር ዋጋ አስከፍለውታል። ነገር ግን ለዘመናት በአንድ ጨቋኝ አገዛዝ ሥር ከመቀመጥ የተከፈለው ወጋ ተከፍሎ መሠረታዊ ለውጥ ለአንድ ማሕበረሰብ ማምጣት ይቻላልም ይሻላልም ተብለው የተደረጉ ናቸው።

አሁን ያለው የኢትዮጵያ መንግሥት በኢትዮጵያ ውስጥ በተካሄደው አብዮት ውስጥ ራሱ ድርሻ ነበረው። ደርግም ኾነ የንጉሡ ሥርዐት ለኢትዮጵያ ማህበረሰብ የሚገቡ አይደሉም ብለው በማመጽ ዓላማቸውን ከግብ አድርሰዋል። ብዙ ዋጋ ተከፍሎበት ለዚህ በቅተዋል። ነገር ግን ከሁለት ዐሥርት ዓመታት የሥልጣን ቆይታ በሁዋላ ልክ እንደ ደርግ “አምጻለሁ ብትል እጨፈልቃኻለሁ” የሚል የዶክመንታሪ መልእክት ያስተላልፉልናል። በሥልጣን ርካብ ላይና በአገሪቱ ገንዘብ ካዝና ላይ የተቀመጣችኹ ኾይ! እናንተ የንጉሡና የደርግ ሥርዐት እንዳንገሸገሻችሁ ሁሉ፤ አሁንም በእናንተ ሥርዐት የሚንገሸገሹ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሕዝቦችን አፍርታችሁዋል። ጭቆናችሁ እና ጭካኔያችሁ አንገፍግፎታል፤ ጭቆና እስካለ ድረስ ምንጊዜም ዐመጽ ይኖራል፤ ለእኔ በግሌ በቅርብ የሚከሰት “የጥራጥሬም፣ የፍራፍሬም፣ የቀለምም” አብዮት ያለ ባይመስለኝም፤ እናንተን ከእንቅልፋችሁ እያባነነ አስቸግሯችሁ ይኼን ዶክመንተሪ ስላሠራችሁ ማመስገኑ ተገቢ ሳይኾን አይቀርም።

አብዮት የኢትዮጵያን አንድ ትውልድ እምሽክ አድርጎ በልቶብናል፤ የዚያን ትውልድ ክፍተት ለመሙላት በሚማስነው በዚህ አዲስ ትውልድ ላይ ሌላ አብዮት አትፍጠሩበት። አብዮት እንዲመጣም ኾነ እንዲፈጠር የሚያደርገው ፍጹም አምባገነን የኾነ ሥርዐት ነው። ጥያቄውን ወደ ሕዝቡ ከመወርወር በፊት ወደራሳችኹ መልሱት። እንደኔ ግምት የማንኛውም ኢትዮጵያዊ ጥያቄ ፍትህን፣ እኩልነትንና ነጻነትን የሚያሰፍን ሥርዐት ይፈጠር የሚል ነው። ለእነዚህ ሦስት መስፈሪያዎች የሚኾን መልስ ካላችሁ ወላ የጥራጥሬ፣ ወላ የፍራፍሬ፣ ወላ የቀለም የሚባል አብዮት አያሳስባችሁም። ዶሮዋን አታታሏት፤ በመጫኛም አትጣሏት!!

No comments:

Post a Comment