በደሴ ሚሊየኖች የመሬት ባለቤት እንሁን ሲሉ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ጩኽዋል።መሬት ክብር ነው። መሬት ሃብት ነው። መሬት ማንነትም ነው። ይህ ክብር፤ ይህ ሃብት፤ ይህ ማንነት ከህዝቡ ላይ ተወስዷል። በኢትዮጵያ ውስጥ የመሬቱ ባለቤት ህወሃት-ኢሕአዴግ ነው። ይሄ ቡድን መሬቱን ብቻ ሳይሆን ህዝቡንም “የእኔ ንብረት ነው” የሚል አስተሳሰብ አሳድሯል። በዚህ አስተሳሰቡም የወደደውን ሲተክል፤ የጠላውን ሲነቅል ብዙ ዓመት ኑሯል። ከዝያም “ህዝቡ ተኛ ብንለው ይተኛል፤ ተነስ ስንለውም ይነሳል” እያለም ይሳለቃል። እውነት ነው መሬት አልባ የሆነ ዜጋ ተኛ ሲባል ከመተኛት፤ ተነስ ሲባልም ከመነሳት ሌላ ምን የተሻለ አማራጭ አለው? ለዚህ አማራጭ ላጣ ህዝብ አማራጭ ይኖረው ዘንድ የምትተጉ ወገኖችን ከልብ እናደንቃለን።
የደሴውን ሰልፍ ያዘጋጃችሁ ዜጎች ተስፋ አለመቁረጣችሁ ይደነቃል። ከፍ አድርጋችሁ የጮኻችሁት ጩኽት በኢትዮጵያ ውስጥ ከዳር አሰክ ዳር ተስተጋብቷል። ይሄን ድምፅ ያልሰማው ህወሃት-ኢሕአዴግ ብቻ ነው። ይሄ ቡድን “ማን አባቱ ይጠይቀኛል” የሚል ከንቱ እብሪት ዓይኖቹ እንዳያዩ፤ ጆሮዎቹም እንዳይሰሙ ስላገዱት የሰልፉን ድምፅ አላየሁምም አልሰማሁምም ብሏል። ህወሃት ማስተዋል የሚችል ቢሆን ኑሮ ይሄን ድምፅ አድምጦ መልስ ቢሰጥ እንደሚበጀው ያውቅ ነበር። ግን ምን ያደርጋል “እኔ ከሞትኩ ሠርዶ አይበቀል” የምትለዋን እንስሳ መምሰልን የመረጠ ቡድን በመሆኑ ይሄን መሰሉን ድምፅ ሲሰማ “እኔ የኢያሪኮ ግንብ አይደለሁም በጩኸት የምናደው ” እያለ ይሳለቃል።እንዲያውም “የእኔን ፖሊስ ማስቀየር የሚቻለው በመቃብሬ ላይ ነው” እያለ እንደሚፎክርም መታወቅ አለበት።
ህወሃት-ኢሕአዴግ መንግስት ሊሸከመው የሚገባውን አገራዊ ኃላፊነት ለመሸከም ብቃት ያለው ቡድን አይደለም። ይሄ ቡድን የመንግስት ቅርፅና መልክ የለውም። የዚህ ቡድን መልኩና ቅርፁ “የመርሲነሪስ” መልክና ቅርፅ ነው። ይህን መልክና ቅርፅ የያዘን ቡድን ነጭ ሪባን እያውለበለብኩ ከያዘው የጥፋት ጎዳና እመልሰዋለሁ ብሎ ማመን ለእኛ የሚቻል አይደለም። የማይቻለውን ይቻላል ብላችሁ የተነሳችሁ ወገኖች ትዕግስታችሁን እናደንቃለን። ህወሃት ከሆነው ወይም ከተናገረው ውጪ ሌላ ስብዕና የለውም። የያዝኩት የጥፋት መንገድ የሚቀየረው በመቃብሬ ላይ ነው፤ ፖሊሲየን ለማስቀየር የሚፈልግ ካለም በሊማሊሞ በኩል ብቅ ይበል ማለቱ እውነት ነው። እኛ ይሄን እውነት አምነናል። የእናንተን ትጋትና ት ዕግስት ግን ከልብ እናደንቃለን።
ሠላማዊ ሠልፍ ማድረግ የዜጎች የማይገሰሰ መብት ነበር። ህወሃቶች ፅፈው ለህዝቡ የሰጡት ህግ መንግስትም ይሄን ይመስከራል። ሠላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ማሳወቅ እንጂ ፈቃድ መጠየቅ አያሰፈልግም የሚል ህግም አለ። ህወሃት-ኢሕአዴጎች ግን በዚህ ቀን አልፈቀድንም፤ በዚህ አካባቢ ከልክለናል እያሉ ራሳቸው የሠሩትን ህግ ከአፈር ይቀላቅሉታል። በዚህም የዜጎችን የመሰብሰብ መብት ይጥሳሉ። ጣሊያኖች በአገራችን በቆዩባት በዚያች አጭር ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያዊያንን በዚህ በኩል አትለፉ፤ በዚያ በታች በኩል ሂዱ እያሉ ያንገላቱ ነበር። ህወሃት-ኢሕአዴጎችም ቀኝ ገዢዎች የሚፈፅሙትን ዓይነት አድሎ በዜጎች ላይ እየፈፀሙ ይገኛሉ። ኢትዮጵያዊያን በመስቀል አደባባይ መስበስብ ሲከለከሉ፤ ህወሃት-ኢሕአዴጋዊያን ግን በመስቀል አደባባይ ከበሯቸውን እየደለቁ በደስታ ይጨፍሩበታል ማንስ ይከለክለናል እያሉ ያዜሙበታል።
እንግዲህ እንዲህ ዓይነቱን ክፉና ዘረኛ ቡድንን በሰላም አደብ ለማስገዛት የምትጥሩ ወገኖች በርቱ።ባለፈው በባህር ዳር የተደረገው የተቃውሞ ሠልፍ በግሩም ሁኔታ ተጠናቋል። ከባዶ ጭንቅላት ባዶ እግር እንደሚሻልም አስተምሯል። ከሠልፉ በኋላ መንግስት ነኝ ከሚለው አካል የተሰጠ መልስ የለም።ዓለምነህ መኮንን ግን እሰከ አሁን በወንበሩ ላይ አለ። አሁን ደግሞ በደሴ “ የሚሊየኖች ድምፅ ለመሬት ባለቤትነት” በሚል መሪ ቃል ሠልፍ ተደርጓል። ይሄም በግሩም ሁኔታ ተጠናቋል። አሁንም መልስ የሚሰጥ አካል ብቅ አለማለት ብቻ ሳይሆን ሠልፉን የሰማም አይመስልም። ነገ ደግሞ በአዲስ አበባና በሌሎች አካባቢ ሌላ ሰልፍ ይደረጋል።ይሄም ግሩም ሃሳብ ነው።ከሰልፉ በኋላ የህዝቡን ሮሮ ሰምቶ መልስ የሚሰጥ አካል ይኖር እንደሆነ አብረን እናያለን።
ኢትዮጵያዊያን መከራችን ቡዙ ነው።ዋነኛው የመከራችን ምንጭ ግን ህወሃት-ኢሕአዴግ ነው። በአሁን ሠዓት በኢትዮጵያችን ከተጋረጠው ችጋር በላይ ችግር የሚሆንብን ህወሃት ነው። ይሄ ዘረኛ ቡድን የመከላከያ ኃይሉን፤ የደህንነት ተቋሙን፤ የንግድ አምባዎችን ያቆመበት መሠረት ከሶሪያው አሳድ አገዛዝ ጋር አንድ ነው። ዛሬ ሶሪያ የገባችበት መከራ በቀላሉ የሚቋጭ አልሆነም። ምክንያቱም የስልጣኑን እርከን የተቆጣጠሩት ቡድኖች መሠረታቸውን ያቆሙት በጎሳ ላይ በመሆኑ ነው። የህወሃት መሠረቱ ጎሳ ነው። በጎሳ ተደራጅቶ የሌላውን ጎሳ ሲያንገላታ እነሆ ሁለት አሥርተ ዓመታት ሞላው። በጎሳ ተደራጅቶ ሌላውን ሲዘርፍ ብዙ ዓመት ተቆጠረ። ሌላው ጦሙን ሲያድር እርሱ ብቻ በልቶ የሚያድር ሆነ። የሌላው ልጅ በበርሃ ቀልጦ ሲቀር፤ ገሚሱ የአዞ እራት ሲሆን የእርሱ ልጆች ግን በአውሮፓና በአሜሪካን ለትምህርት የሚላኩ ሆኑ። በህወሃት የሚፈፀመውን አድልዎ በቃል ለመግለፅ ከምንችለው በላይ ነው። እንዲህ መሠረቱን በአድልዎና በጎሳ ላይ ያቆመ ቡድንን ከተቆናጠጠበት የዝሪፊያ ወንበር ላይ ለማውረድ የሚጠይቀው መሥዋዕትነት በቀላሉ የሚገመት አይሆንም። እስከ አሁንም ብዙ መሥዋዕትነት ተከፍሏል። ገና ወደፊትም ብዙ መሥዋዕትነት ይጠይቃል። ለዚህ ራስን በቅጡ አደራጅቶና ተባብሮ መታገል ግዜው የሚጠይቀው ታሪካዊ ግዴታ ሁኗል።
የመንግስት ሳይሆን የወሮ በላ መልክና ቅርፅ ካለው ቡድን ፊለፊት ቆማችሁ በየቦታው የምታሰሙት የተቃውሞ ድምፅ መልካም ነው።ብዙ መሥዋዕትነትም እያሰከፈላችሁ እንደሆነ እንገነዘባለን። ይሄ የምትከፍሉት መሥዋዕትነት በከንቱ እንዳይሆን ግን አጥብቆ ማሰብ ይገባል። እስከ አሁን ብዙ ጥያቄዎች ተነስተዋል። የአማራን ህዝብ ያዋረደው ግለሰብ ለፍርድ ይቅረብ የሚል ድምፅ በባህር ዳር ተስተጋብቷል። የአማራን ህዝብ የሰደበው ግለሰብ ግን እኔ አልተሳደብኩም፤ ተቃዋሚዎች ቆርጠው ቀጥለው ያቀረቡት ነው እያለ ይሳለቃል። በሌላ በኩል ደግሞ በከተማዋ ውስጥ ያሉትን ኮምፒውተሮች ለቃቅሞ መረጃውን የላከውን ዜጋ ፍለጋ ሌሎች ዜጎችን እያሰቃየ ይገኛል። ይህን መሰሉን ንቀት ልንሸከም አይገባንም። ህወሃት-ኢሕ አዴጎች ለህዝብ ጥያቄ መልስ እንዳይሰጡ ያደረጋቸው ምን እንደሆነ እንደገና መጠየቅ ይኖርበታል። የሚመራውን ህዝብ የሰደበ ግለሰብ ለፍርድ መቅረቡ አግባብ ነው። ይሄ ስደብ ግን የግለሰብ አፍ ወለምታ ሳይሆን የድርጅቱ አቋም ነው። ድርጅቱ ለፍርድ ሊቀርብ አይችልም። አዎን ኢሕኢደግ አይከሰሰም፤ ሰማይም አይታረስም የሚል ተረት አላቸው። እንግዲህ ምን ይሻላል? ይሄ ዘረኛና ዘራፊ ቡድን ትክክለኛውን መልስ እስኪሰጥ ድረስ ትግሉ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል። ትክክለኛዋ መልስ ደግሞ ሰዳቢው ለፍርድ መቅረብ ብቻ ሳይሆን ፍትህ፤ እኩልነት እና ነፃነት በዚያች አገር ነግሰው መታየት ነው።
የተከበራችሁ ያገራችን ዜጎች አገራችን ያለችበት ችግር ከእሪታ በላይ ነው። እሪ ብንልም የሚሰማ መንግስት የለንም። የሚሰማ መንግስት የለም ተብሎ ዝም ማለት ግን ትክክለኛ ምርጫ አይደለም። በሚቻለው መንገድ ሁሉ በጫንቃችን ላይ ቁጢጢ ያሉ ወሮበላዎችን ማስወገድ ግድ ነው። ህወሃት-ኢህአዴጎች ሳይፈለጉ በዜጎች ጫንቃ ላይ ቁጢጢ ብለው ሃያ ዓመት አለፋቸው።”ሳንፈልጋቸው ሃያ ዓመታቸው” የሚባል ቅኔ ቢዘረፍላቸውም አልገባቸውም። የእነርሱ ምኞት ሌላውን ሁሉ እንደ ሰም አቅልጦ፤ እንደብረት ቀጥቅጦ መግዛት ነው። ሁል ግዜ እነርሱ ከላይ፤ ሌላው ሁሉ ከታች እነርሱን ተሸክሞ እንዲኖር ብርቱ ምኞት አላቸው። ይሄንንም እውን ለማድረግ ራሳቸውን ህግ አድርገው ቀርፀዋል። የአገሪቷም ፍትህ በእነርሱ ስሜት እየተወሰነ ዜጎችን ለማጥቂያነት ውሏል። የፍትሁን ሥርዓት አፈር ከድሜ ካስገቡት በኋላ ሰለዴሞክራሲ ሊነግሩን ሲነሱ የዓይናቸው ሽፋሽፍት እንኳ አይርገበገብም። እነዚህ ቡድኖች ጭካኔን ከጀግንነት መለየት የማይችሉ ፍፁም ርህራሄ የሌላቸው ናቸው። ይሄን ቡድን ነጭ ሪባን እያውለበለቡ ከተቆናጠጡበት ወንበር የማውረዱ ትግል ቢሳካ ለሁላችንም እፎይታ ይሆን ነበር።እኛ ግን ህወሃት-ኢሕአዴግ በሠላማዊ መንገድ ስልጣኑን ለህዝብ ያስረክባል የሚል እምነት የለንም።
የተከበራችሁ ወገኖቻችን !
እንግዲህ እናንተም በያዛችሁት መንገድ እንዲሳካላችሁ እንመኛለን። እኛም በአገራችን ፍትህ፤ እኩልነት እና ሙሉ ነፃነት እስከሚሰፍን ድረስ የጀመርነውን ትግል አጠናክረን እንቀጥላለን። የእኛም ሆነ የእናንተ መዳረሻ ግቡ አንድና አንድ ነው። አገራችን ከዘረኞችና ከዘራፊዎች ፀድታ፤ ፍትህ እኩልነትና ነፃነት ነግሶ፤ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ተገንብቶ እና ሠላም ሠፍኖ ማየት ነው ግባችን።እኛ በሊማሊሞ በኩል ብቅ በሉ ያሉትን ሰምተን በዚያው አያቶቻችን ባለፉበት የነፃነት መንገድ ልንጓዝ ስንቃችንን እያሰናዳን ነው። የአያቶቻችንን ጋሻና ጦር ከተሰቀለበት አውርደን እየወለወልን ነው። ከእንግዲህ ወዲያ ከህወሃት-ኢሕአዴግ የምንጠብቀው ምንም በጎ ነገር የለም። እነርሱ ተጭነውን፤ እኛ ተሸክመናቸው ለዘላለም አንኖርም። እነርሱ ሰጪ እኛ ተቀባይ፤ እነርሱ ፈቃድ ሰጪ እነርሱ ፈቃድ ከልካይ ሆነን ለዘላለም አንኖርም። ለነፃነት የሚከፈለውን ማንኛውንም መሥዋዕትነት ለመክፈል ሳናቅማማ ተነስተናል።
በመጨረሻም ለህወሃቶች እንዲህ እንላችኋለን “ነፃነታችንን ስጡን ወይም ነፍሳችንን እንኳት” አበቃን።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!
No comments:
Post a Comment