Wednesday, June 26, 2013
ወያኔ ሕወሃት የደደቢቱን አስታውስ!
በሚያስደንቀው የሀገራችን ምርጫና ከዚሁ የምርጫ ሳጥን በሚገኝ የሕዝብ ድምጽ፤ በሰላማዊ መንገድ ወያኔ ሕወሃትን እናሸንፋለን ብለው ቀን ከሌት ከሚደክሙትም ሆነ ሰላማዊው አማራጭ አዋጭ አይደለም በማለት በነፍጥ ወያኔን ለማንበርከክ እየታገሉ ያሉ ኢተዮጵያዊ የፖለቲካ ፓርቲዎችንም ሆነ ድርጅቶችን በሀገር ፍቅር ማጣትም ሆነ ተቆርቋሪነት፣ በሕዝብ ክብር መጉደልም ሆነ ሀላፊነትን መዘንጋት ለመውቀስ የሚያበቃ የሞራል ልዕልና ወያኔ ሕወሃት የለውም። ሌላው ቀርቶ በጫካ ዘመን አስተሳሰቡና ምግባሩ ይቅርና መንግስት ነኝ ካለ በሗላ ባሳያቸውና እያሳያቸው ባሉት ምግባሮቹ እንኳ ቢገመገም በሀገራችን ካሉት ሀገራዊም ሆኑ ክልላዊ ፓርቲዎች እንዲሁም በነፍጥ እየታገሉ ካሉት ድርጅቶችና ንቅናቄዎች ጋር ለመወዳደር የሚያበቃ ተክለ ሰውነት እንዲሁም የሀገርና የሕዝብ ፍቅር አልታየበትም።
እነዚህን ፓርቲዎች ወይም ድርጅቶች አንድ ጊዜ የሀገራችንን ጥቅም አሳልፈው የሸጡና ከአሸባሪ ጋር የወገኑ ሌላ ጊዜ ከሀገራችን ታሪካዊ ጠላቶች ጋር ያበሩና ሀገር ለማፈራረስ የተዘጋጁ እያለ ለመክሰስ እራሱ ወያኔ ሕወሃት ማነው? እንዴትስ አሁን ላለበት የገዥነት ወንበር በቃ? በነማን እርዳትነት? አሁንስ ስለ ሀገራችንና ሕዝባችን ያለው አመለካከት ምንድን ነው? እና የመሳሰሉትን ጥያቄዎች መመልከት ተገቢ ይሆናል።
በመጀመሪያ ደረጃ ለሕዝባችን በሰላማዊም ሆነ በሌላ አማራጭ እየታገሉ ካሉት ድርጅቶች ፍጹም የተለየ በነበረው እንቅስቃሴው በዓለም አቀፍ ደረጃ አሸባሪ ተብሎ ተፈርጆ የሀገራችን ማፈሪያ የነበረው ድርጅት ራሱ ወያኔ ሕወሃት እንጅ ሌሎች የሀገራችን ፓርቲዎች ድርጅቶች ወይም ንቅናቄዎች አልነበሩም። የህ የወገንና የሀገር ማፈሪያ የሆነው ቡድን ወያኔ ሕወሃት በተለይ ከ1968 እስ 1982 ዓ/ም በነበሩት ዓመታት በሕዝባችንና በሀገራችን ላይ በፈጸማቸው አስር የከፉ የአሸባሪነት ስራዎች ምክንያት ስሙ በዓለም አቀፉ የአሸባሪዎች ዳታ ቤዝ ተመዝግቦ ይገኛል። “የሌባ ዓይነ ደረቅ መልሶ ልብ ያደርቅ” እንደሚባለው ሆነና ዛሬ ግን ራሱ ተመልሶ እንደፈለገ በሚያዘው ፓርላማው በመጠቀም ስለ ሕዝባቸው አርነት ስለ ሀገራቸው ነጻነት እየታገሉ ያሉ ድርጅቶችን አሸባሪ የማያስቡና ለሕዝባቸው ደንታ የሌላቸው ለማለት በቃ።
ዛሬ በሂወት የሌሉትም ሆኑ በአካለ ስጋ የሚንጠራወዙት አብዛኞቹ የወያኔ ቁንጮዎች ያኔ በጫካ ዘመናቸው በዓለም ዙሪያ ለልመና ይንቀሳቀሱ የነበሩት የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላት ከነበረችው ሶማሊያ ጋር በማበርና ከሶማሊያ በተገኘ ፓስ ፖርት በመጠቀም እንደነበር ሲታወስ ወያኔ ሕወሃት በተቃዋሚዎች ላይ አፉን ለማላቀቅ ምን የሞራል ብቃት አለው? ያስብላል። ከዚህ በተጨማሪም ከጎረቤት ሱዳንና ግብጽን ጨምሮ ከአብዛኞቹ አረብ ሀገሮች ከፍተኛ እርዳት ይፈስለት የነበረው ወያኔ ሕወሃት ከታሪካዊ ጠላታችን ሱዳን ግዛት እየተንደረደረም የሽብር ጥቃቱን በሕዝባችን ላይ ይፈጽም እንደነበር መቼም የማንረሳው የሃዘን ትዝታችን ነው። ይህንን የሱዳን እርዳታም ከውሌታ በመቁጠር ይመስላል ርዝመቱ 1600 ኪሎ ሜትር ስፋቱ ደግሞ እስከ 60 ኪሎ ሜትር የሚደርሰውን ሰፊና ለም የሀገራችንን መሬት ቆርሶ ለሱዳን ማስረከቡስ ምናልባት ከሀገር ፍቅርና ወዳድነት ለወገን ክብርና ሞገስ ከማሰብ ይሆን ይሆን?
ከወያኔ ሕወሃት በፊት የነበረው አንባገነን ገዥ ደርግ በድንበር ይገባኛል ምክንያት በ1969 ዓ/ም ሀገራችንን በግፍ ወርራ ከነበረችው ሶማሊያ ጋር ጦርነት ገጥመን በነበረበት ወቅት ከጠላት ጋር በማበር ሀገራችንንና ሕዝባችንን ከሌላ አቅጣጫ ይወጉትና ያሰቃዩት የነበሩት እነዚሁ ያዛሬዎቹ ጉዶች ወያኔ ሕወሃቶች ለመሆናቸው የታሪክ መዛግብቶች ያስረዳሉ። ሌሎች የሀገራችን ሰላማዊም ሆኑ በሌላ አማራጭ ወያኔን ለመታገል የወሰኑት የዛሬዎቹ ድርጅቶች ግን በእንዲህ አይነት ቅሌት በማስረጃ በተደገፈ መልኩ አንዳቸውም ሲታሙ አልሰማንም። ሕዝባችንን ያለማቋረጥ እየወጋ ካለው ወያኔ ሕወሃት ጋር ከሚያደርጉት ትግል በስተቀር።
ጥቁር ሕዝብ ነጭን ሊያሸንፍ አይችልም የሚለውን የተሸናፊነት መንፈስ ጣሊያንን በተደጋጋሚ በመንበርከክ ለዓለም አዲስ ምእራፍ የከፈተችና የጥቁር ሕዝቦች ኩራት የሆነችን ሀገራችንን ልጆቿ ነን የሚሉት ወያኔዎች ግን አፋቸውን ሞልተው “ኢትዮጵያ በታሪኳ አንድም ጦርነት አሸንፋ አታውቅም” በማለት ዓለም የሚያውቀውን ድንቅ ታሪካችንን ሲያራክሱና የሀገራቸንን ማንነትና የሕዝባችንን ጥንካሬ ብዙ ጊዜ ለማንኳሰስ ሲሞክሩ ታይተዋል። ከዚህም በተጨማሪ በዓመተ ዓለም በሽህ የሚቆጠሩ ዘመናትን በሀገርነት ያሳለፈችውንና በዓመተ ምህረትም ላለፉት ሁለት ሽህ ዓመታት በሀገርነት የምትታወቀዋን ክቡር እድሜ ጠገብ ሀገራችንን ጎማምደው የመቶ ዓመት ያገር ጎረምሳ በማድረግም ወያኔ ሕወሃትን የመሰለ እኩይ ጎጠኛ ቡድን የትም አልታየም። ዛሬ የምናውቃቸው የሀገራችን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ድርጅቶችና ንቅናቄዎች ግን በእንዲህ ያለው ጉዳይ ሲታሙ ተሰምቶ አይታወቅም።
ባንዲራችን የሀገራችን መለያ ነው። ባንዲራችን ሕዝባችንን አንድ አድርጎ ባንድ ላይ ለማሰለፍ የሚጠቅመን የራሱ ትርጉም ያለው የሁላችን ማስተሳሰሪያ ምናባዊ ገመድ ነው። በተለይ በሀገራችን ደግሞ ለባንዲራ ያለን ክብርና ፍርሃት ከፍተኛ በመሆኑ ጥጋበኛን ለማረቅና ለማስተካከል “በባንዲራችን ይዠሃለሁ” እና “በባንዲራችን አምላክ” እየተባለ እስከመለመንና እስከመገዘት የደረሰ ክብር አለው- ባንዲራ። ወያኔ ሕወሃት ግን ይህን ያህል ክብር የምንሰጠውን የሀገራችንን መለያ የሕዝባችንን የአንድነት መታወቂያ እጅግ በጣም አዋርዶና ክብሩን ዝቅ አድርጎ እነደጨው መቋጠሪያ የጨርቅ ቁራጭ ነው ሲል እራሱን በጣም ያዋርዳል ዝቅ ያደርጋል እንጅ ሌላ የፖለቲካ ጥቅም አያገኝበትም አላገኘበትምም። ባንዲራ የጨርቅ ቁራጭ ነው በተባለበት ወቅት ስለባንዲራ ክብር ይከራከሩ የነበሩትን የአንድነት ሃይሎች አፍ ለማዘጋት ተብሎ የተነገረው ንግግር ውሎ አድሮ ወያኔ ሕወሃትን ዋጋ እያስከፈለው መሆኑን አሁን እያየን ነው። በሰላም የሚታገሉትም ሆኑ ነፍጥ ያነገቡት የሀገራችን የፖለቲካ ድርጅቶች ግን ለሀገራችን ባንዲራ ክብር በመስጠት የወያኔን አፍራሽ አባባል ታገሉት እንጅ ይህን በተመለከተም ጉዳይ ቢሆን በአፍራሽነትና በጠላትነት ሲሰለፉ አልታዩም።
ወያኔ ሕወሃት በውይይት ሞቅታ ወይም ሆን ብሎ በማንአለብኝነት አለዚያም ለሕዝባችን ያለውን ንቀት ለማሳት በሚመስል መልኩ አንዱን ካንዱ ለማበላለጥና ለማጋጨት ባለው ፍላጎትና ጥረት ሀገር እየመራሁ ነው በሚልበት ጊዜ እንኳ እጅግ ከመጠን በላይ ጠቦ ተፈጠርኩበት የሚለውን አካባቢ ብቻ በማወደስ “እንኳን ከናንተ ተፈጠርን” እስከማለት የደረሰ ጎጠኛና የማያስብ ጠባብ ቡድን ሀገር ከመምራት ደረጃ ያልደረሱትን ተቃዋሚዎች በሃላፊነትና ተጠያቂነት እጥረት ለመክሰስ የሚያስችል የሞራል ብቃት የለውም።
ከዚህም እጅግ በከፋ መልኩ የሀገርን አንድነትና ሉአላዊነት ለማስከበር ለዘመናት በፍቅርና በመከባበር ላይ ታች ሲል የኖረውን የኢትዮጵያን ሕዝብ አንድነት ለመናድና “የኔ አይደለም” ወይም “የኛ አይደለም” የሚለውን መጥፎ ስሜት በሕዝባችን ውስጥ ላማስገባት ሲል “ ትግሬዎች አክሱም አላቸው ይህ ለጉራጌው ምኑ ነው? አገዎች ላሊበላ አላቸው ይህ ለኦሮሞው ምኑ ነው? ጎንደሮች ቤተ መንግስት አላቸው ይህ ለወላይታ ምኑ ነው” በማለት ልዩነትን የሰበከው፣ አለመቻቻልን ያወጀው፣ የበላይና የበታችነትን ያስተማረው ወያኔ ሕወሃት በምን ሞራል ልዕልናው ነው ሌሎችን ተቃዋሚዎች የሀገርን ሉአላዊነት በመጋፋትና ለሕዝብ ፍቅር በማጣት ሊከስ የሚችለው?
አንድ አካል ወይም ቡድን በተለይም እንደ ወያኔ ሕወሃት አይነት በእኩይነቱ በዓለም ደረጃ የሚታወቅ ቡድን፤ የመጣባቸው መንገዶች፣ ያልደበዘዙት ዱካዎቹ እንዲሁም ያሁን ማንነቱ አፍ አውጥተው እሱነቱን እያሳበቁበት ይቅርና ራሱን የደበቀ ድርጅት ቢሆን እንኳ “እኔ ጥሩ ነኝ ስላለ ጥሩ የሚሆን፣ ሌሎች መጥፎ ናቸው ስላለም ሌላው ተከጥሎ መጥፎ የሚልለት አይደለም”። ሁሉም በሚሰራው ይመዘናል። በሰራውም ተቀባይነትን ሊያገኝ ወይም ሊያጣ ይችላል እንጅ ሕዝብ ዝም ብሎ በስማ በለው አይጥልም አያከብርምም። “ለቀባሪው አረዱት” እንዳይሆንብኝ እንጅ በተለይም እንደ ወያኔ ሕወሃት አይነት ጎጠኛ ቡድን በኢትኦጵያ ሕዝብ ክብር ካጣ የቆየ በመሆኑ ተቀባይነቱም በዚያው መጠን የወረደ ነው።
ስለሆነም “ሌባ እናት ልጇን አታምንም” ሆኖበት ራሱ ሲያደርገው የነበረውን የሽብር ስራ ሁሉ ሌሎች ተቃዋሚ ድርጅቶች ሊያደርጉት ይችላሉ ብሎ በመጠርጠር የራሱን ግልባጭ እነ እንቶኔ አደረጉ ወይም ሊያደርጉ ነው። ከጠላትችን ከእንቶኔ ጋር ሊተባበሩ ነው፣ የሀገራችን ጠላት እንቶኔ አስተባብሮና አደራጅቶ ሊልክብኝ ነው እና የመሳሰሉትን በማውራት እትት ሲል ከርሟል። ወያኔ ሕወሃት እያወራው ያለው እውነትም ይሁን ውሸት ይህን ነጥብ በተለይ አንስቶ በሀገር ፍቅርና ተቆርቋሪነት ጉዳይ የሀገራችንን ተቃዋሚዎች የታጠቁም ይሁኑ ሰላማዊ ፓርቲዎችን ለመውቀስም ሆነ ለመክሰስ ወያኔ ሕወሃት የሞራል ልዕልና ይጎድለዋል። ብቃትም የለውም።
በይኸነው ዓለሙ
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment